Media Center



Post Date: 05 Jul 2024

Post Date: 27 Nov 2023

Post Date: 04 Nov 2023

Post Date: 15 Oct 2023

Post Date: 11 Oct 2022

Post Date: 06 Sep 2022

Post Date: 30 Aug 2022

Post Date: 25 Sep 2021

Post Date: 15 Jan 2021

Post Date: 11 Dec 2020

Post Date: 11 Dec 2020

Post Date: 02 Sep 2020

Post Date: 05 Mar 2019

Post Date: 05 Mar 2019

Post Date: 27 Feb 2019

ቡና ኢንሹራንስ አ.ማ ያልተጣራ 59.4 ሚሊዮን ብር አተረፈ

የዓመቱ የካሳ ክፍያ ወጪና መጠባበቂያ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል በተጠናቀቀው የ2015 የሒሳብ ዓመት 902.7 ሚሊዮን ብር የዓረቦን ገቢ ማሰባሰብ የቻለው ቡና ኢንሹራንስ ለዓመቱ ይዞት ከነበረው ዕቅድ ቅናሽ የታየበት ያልተጣራ 59.4 ሚሊዮን ብር አተረፈ። ቡና ኢንሹራንስ ሕይወት ነክ ካልሆነው የኢንሹራንስ ዘርፍ ያገኘው የዓረቦን ገቢ ለዓመቱ ከያዘው ዕቅድም ሆነ ከ2014 የሒሳብ ዓመት ከፍተኛ ብልጫ ያሳየ ስኬት አስመዝግቧል።

የቡና ኢንሹራንስ ኩባንያ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ አበረ ምሕረቱ ሰሞኑን በተካሄደው የኩባንያው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ባቀረቡት ሪፖርት፣ ኢንሹራንስ ኩባንያ በሒሳብ ዓመቱ ካገኘው 902.7 ሚሊዮን ብር አጠቃላይ የዓረቦን ገቢው ውስጥ 880 ሚሊዮን ብር የሚሆነው ሕይወት ነክ ካልሆነው የኢንሹራንስ ዘርፍ እንደተገኘ ገልጸዋል። ይህም ኩባንያው በሒሳብ ዓመቱ አገኛለሁ ብሎ ካቀደው 527.16 ሚሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር የ67 በመቶ ብልጫ አለው ብለዋል፡፡

ኩባንያው ከዚሁ ሕይወት ነክ ካልሆነው የኢንሹራንስ ዘርፍ በ2014 የሒሳብ ዓመት አግኝቶት ከነበረው 468.7 ሚሊዮን ብር የዓረቦን ገቢ ጋር ሲነፃፀር በተጠናቀቀው የ2015 ሒሳብ ዓመት የተገኘው የዓረቦን ገቢ የ88 በመቶ ብልጫ እንዳለው ገልጸዋል፡፡ በተመሳሳይ በሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፉም ኩባንያው በ2015 የሒሳብ ዓመት 22.54 ሚሊዮን ብር ዓረቦን መሰብሰብ ችሏል፡፡ ከሕይወት ኢንሹራንስ ማሰባሰብ የቻለው ዓረቦን ከዕቅዱ አንፃር የ75.51 በመቶ ብልጫ ያለው ሲሆን፣ በ2015 የሒሳብ ዓመት ዕቅዱ አንፃር ደግሞ አፈጻጸሙ በ12.84 ሚሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው ተጠቅሷል፡፡ በሒሳብ ዓመቱ ኩባንያው ካሰባሰበው ጠቅላላ ዓረቦን ውስጥ 64 በመቶ ከተሽከርካሪ ዋስትና የተሰባሰበ ሲሆን፣ 21 በመቶው ደግሞ ከሕጋዊ ኃላፊነት የመድን ሽፋን፣ ዘጠኝ በመቶው ከፖለቲካዊ አመፅና ሽብር ኢንሹራንስ ሽፋን የተሰባሰበ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ቀሪው ከተለያዩ የመድን ሽፋኖች የተገኘ የዓረቦን ገቢ ነው፡፡ በሒሳብ ዓመቱ ኩባንያው የተጣራ 295.37 ሚሊዮን ብር ለካሳ ክፍያ ወጪ ማድረጉንና በእንጥልጥል ለሚገኙ የካሳ ክፍያ ጥያቄዎች ደግሞ 189.34 ሚሊዮን ብር መጠባበቂያ መያዙ ታውቋል። ኩባንያው በ2015 የሒሰብ ዓመት ወጪ ያደረገው የተጣራ የካሳ ክፍያ ከዕቅዱ በ30.52 በመቶ ከፍ ያለ ሲሆን፣ በመጠባበቂያነት የያዘው የካሳ ክፍያ መጠንም በተመሰሳሳይ ከዕቅዱ በ67.42 ብልጫ ማሳየቱን የቦርድ ሊቀመንበሩ ሪፖርት ያመለክታል፡፡

ኩባንያው የ2015 ሒሳብ ዓመት የተጣራ የካሳ ክፍያ ወጪው 226.31 ሚሊዮን ብር እንደሚሆን፣ በመጠባበቂያነት የሚይዘው የካሳ ክፍያ ወጪ ደግሞ ከ113 ሚሊዮን ብር እንደማይዘል አቅዶ ነበር፡፡ ነገር ግን በሐሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ ከፍተኛ የሚባል የካሳ ክፍያ ወጪና መጠባበቂያ ለመያዝ መገደዱን የኩባንያው የአፈጻጸም ሪፖርት ያመለክታል።

ኩባንያው ከኢንሹራንስ የሥራ ዘርፍ ውጪ ሀብቱን ካፈሰሰባቸው ሌሎች ኢንቨስትመንቶቹ በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ 146.8 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱ በሪፖርቱ ተገልጿል። ከዚህ ውስጥ 58.4 ሚሊዮን ብር የሚሆነው ኩባንያው በተለያዩ ባንኮች ካስቀመጠው ተቀማጭ ገንዘብ የተገኘ የወለድ ገቢ ነው። እስከ ሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ድረስ የኩባንያው አጠቃላይ የኢንቨስትመንት መጠን 545.05 ሚሊዮን ብር መድረሱንም ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡ ከዚህ ውስጥ ከ224.01 ሚሊዮን ብር በተለያዩ ኩባንያዎች ውስጥ ኢንቨስት ያደረገው ሲሆን፣ ቀሪው 321.04 ሚሊዮን ብር ደግሞ በባንክ ተቀማጭ የወለድ ገቢ የሚያገኝበት እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ኢንሹራንስ ኩባንያው በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ ከታክስ በፊት 59.4 ሚሊዮን ብር ትርፍ ያገኘ ሲሆን፣ ከዚህ ትርፍ ውስጥ 52.07 ሚሊዮን ብር የሚሆነው ከጠቅላላ የመድን ሥራ፣ ቀሪው 7.33 ሚሊዮን ብር ደግሞ ከሕይወት የመድን ዘርፍ የተገኘ ስለመሆኑ ተጠቅሷል፡፡

ይህ ትርፍ ግን ኩባንያው በሒሳብ ዓመቱ አገኛለሁ ብሎ ካቀደው 69.4 ሚሊዮን ብር አንፃር የ14.43 በመቶ ከዕቅድ በታች አፈጻጸም ያሳየ ነው፡፡ ከቀዳሚው ዓመት ትርፍ አንፃር ሲታይ ግን በ2015 ሒሳብ ዓመት ያገኘው ትርፍ በ31.72 በመቶ ብልጫ ያለው ሆኗል፡፡ ኩባንያው በቀዳሚው ዓመት አግኝቶት የነበረው ትርፍ 45.08 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ ከቦርድ ሊቀመንበሩ ሪፖርት መረዳት እንደተቻለው፣ በሒሳብ ዓመቱ በኩባንያው ታሪክ ከፍተኛ የሚባለውን የዓረቦን ገቢና ትርፍ ቢያገኝም በሥራ እንቅስቃሴያቸው የተለያዩ ተግዳሮቶቹን ያስተናገዱበት ዓመት መሆኑን ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

በተለይ የፖለቲካ አለመረጋጋትና የሰሜኑ ጦርነትን ተከትሎ የካሳ ጥያቄዎች መቅረባቸውና የተወሰኑት በሕግ ደረጃ ያሉ መሆኑ በዋናነት ተጠቅሷል፡፡ ከዚህም ሌላ በሁሉም የኢኮኖሚ ዘርፎች የንግድ እንቅስቃሴ መቀዛቀዝ፣ እንደ ዩክሬን ያሉ ጦርነቶችና ዓለም አቀፍ የማይመች የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለዘርፉ ማነቆ እንደነበሩ የቦርድ ሊቀመንበሩ ተናግረዋል፡፡ የጋራዥ ባለሙያ የእጅ ዋጋና የመኪና መለዋወጫ ዕቃዎች ዋጋ መጨመር በተቃራኒ ግን የዓረቦን ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ መቀነስ እንደ ተግዳሮት ተጠቅሷል፡፡ የኢትዮጵያ መድን ሰጪዎች ማኅበር አስጠንቶት በነበረው የተሽከርካሪዎች ዝቅተኛ የዓረቦን ተመን ሙሉ በሙሉ አለመተግበሩም እንደ አንድ ችግር በቦርድ ሊቀመንበሩ ቀርቧል፡፡

ኢንዱስትሪው ያጋጠመውን ተግዳሮት በተመለከተ የቡና ኢንሹራንስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዳኛቸው መሐሪ ባስተላለፉት መልዕክትም፣ በዋናነት ከሚጠቀሱ ተግዳሮቶ ውስጥ አንዱ በመድን ኢንዱስትሪ ትክክለኛ በሆነ ፉክክር ምክንያት ከሚገኘው የቀጨጨ ዓረቦን መጠን ጋር ሊወዳደር በማይቻልበት ሁኔታ በዋጋ ግሽበት ምክንያት የተሽከርካሪ መድን የካሳ ወጪ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር ይገኝበታል ብለዋል፡፡ ይህንኑ ተከትሎ ተመጣጣኝ የዓረቦን መጠን እንዲኖር ለማስቻል በኢትዮጵያ መድን ሰጪዎች ማኅበር አማካይነት በውጭ አማካሪ ድርጅት የተጠናውንና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እንዲያውቀው የተደረገውን የተሽከሪዎች ዝቅተኛ የዓረቦን ተመን ተግባር ላይ ለማዋል ተሞክሮ የነበረ ቢሆንም፣ ይህ በሚፈለገው ደረጃ ሊተካከል አለመቻሉን እንደ ተግዳሮት የሚያዩት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ለብሔራዊ ባንክ በቀረበው ጥናት መሠረት የዓረቦን መጠኑ ላለመስተካከሉ ደግሞ በአንዳንድ ኩባንያዎች ትብብር ማነስና ከደንበኞች በቀረበ ቅሬታ መሠረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተጣራው ዝቅተኛ ተመን ሕጋዊ አይደለም በማለቱ ተመኑ ሥራ ላይ ሊውል አለመቻሉ ነው ብለዋል፡፡ የኩባንያው የረዥም ጊዜ ደንበኛ በመሆን ከፍተኛ ዓረቦን ተከፋይ የነበሩ ደንበኞችን አገሪቱ ላይ በነበረው የፖለቲካ ለውጥና ለውጡን ተከትሎ በተከሰቱ የፖለቲካ አለመረጋጋቶች ምክንያት የንግድ እንቅስቃሴያቸው በከፍተኛ ሁኔታ በመዳከሙና የአንዳንዶቹም የመድን ሽፋን በመቋረጡ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው ትልቅ ተግዳሮት ሆኖበት መቆየቱን ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹ከዚህም ሌላ በተለያዩ ተያያዥ ምክንያቶች ያጣውን ገቢ ለመተካት አሁንም ያለው ነባራዊ ሁኔታ ባለመፈቀዱ በሥራችን ላይ ጉልህ አሉታዎች ተፅዕኖ ፈጥሮብናል በማለት፤›› በማለት አቶ ዳኛቸው ያለውን ችግር አብራርተዋል፡፡ በአገሪቱ ያለው የፖለቲካ አለመራጋጋት ለፋይናንስ ዘርፉ በአጠቃላይና በተለይም ለኢንሹራስ ኢንዱትሪው ሌላ ፈታኝ ሁኔታ ሆኖ ስለመቀጠሉ ያወሱት ሥራ አስፈጻሚው፣ በዚህም ምክንያት ደንበኞች እንደገቡት ኢንሹራንስ ሽፋንና ሁኔታዎች የሚስተናገዱ በመሆኑና ይህም እንደ ውሉ ሁኔታ እንጂ እንደ መድን ደንበኞች ፍላጎት ባለመሆኑ በኩባንያው ግንኙነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩ አልቀረም ብለዋል፡፡ ቡና ኢንሹራንስ በአሁኑ ወቅት 233 ሠራተኞች ያሉት ሲሆን፣ ከ33 በላይ ቅርንጫፎች አሉት፡፡ ኩባንያው ጠቅላላ የሀብት መጠኑንም በ91.66 በመቶ በማደግ 2.07 ቢሊዮን ብር ሊደርስ ችሏል፡፡