ቡና ኢንሹራንስ ኩባንያ የትርፍ ምጣኔው ሲቀንስ ገቢው መጨመሩን አስታወቀ
ቡና ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበር በ2012 የሒሳብ ዓመት ከመድን ሥራ ውል ያገኘው የትርፍ መጠን ሲቀንስ ከተለያዩ ኢንቨስትመንቶቹ ያገኘው ገቢ ግን ማደጉን አስታወቀ፡፡ ኩባንያው የ2012 የሒሳብ ዓመት አፈጻጸሙን ይፋ ባደረገበት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ እንደገለጸው፣ በሒሳብ ዓመቱ የመድን ውል ሥራ ያስገኘለት ትርፍ መጠን 27.9 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ ይህ የትርፍ መጠን ከቀዳሚው ዓመት የመድን ውል ሥራ ትርፍ ሲነፃፀር በ6.59 ሚሊዮን ብር ያነሰ ሆኗል፡፡ኩባንያው በ2011 የሒሳብ ዓመት ከመድን ውል ሥራ አግኝቶ የነበረው የትርፍ መጠን 34.44 ሚሊዮን ብር እንደነበር ታውቋል፡፡ በ2012 ደግሞ ከዚሁ ዘርፍ አገኛለሁ ብሎ አ ቅዶ የነበረው 14.9 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ አፈጻጸሙ ከዕቅዱ 66.6 በመቶ ነው፡፡ቡና ኢንሹራንስ ከመድን ውል ሥራ ያገኘው ትርፍ ቅናሽ ሊያሳይ ከቻለባቸው ምክንያቶች በዋነኝነት የተጠቀሰው በተሽከርካሪ የውል ዓይነቶች ምክንያት በተፈጸመ በሕጋዊ ተጠያቂነት ለመጠባ በቂያ የተያዘው የካሳ መጠን በመጨመሩ ነው፡፡ ይህም ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት በኋላ የጭነት ምልልስ መጨመርን ተከትሎ በተከሰቱ በርካታ አደጋዎች ምክንያት እንደሆነም የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዳኛቸው መሐሪ በዓመታዊ ሪፖርታቸው ጠቅሰዋል፡፡ ኩባንያው ከመድን ሥራ ውል ያገኘው ትርፍ ቢቀንስም በሌሎች የገቢ ምንጮች በ22 በመቶ ዕድገት በሒሳብ ዓመቱም ከተለያዩ የገቢ ምንጮች 34.46 ሚሊዮን ብር ገቢ ያገኘ ሲሆን፣ ይህ ገቢ ከዕቅዱ አንፃር ሲታይ 22 በመቶ ብልጫ አለው ተ ብሏል፡፡ ከልዩ ልዩ ገቢዎች ውስጥ በዋናነት የሚጠቀሰው ከጊዜ ገደብ ተቀማጭ ገንዘብና ከመንግሥት የተቀማጭ ቦንድ የተገኘ ወለድ፣ ከተንቀሳቃሽ ቁጠባ የተገኘ ወለድ፣ ከኢንቨስትመንት የተገኘ ትርፍና የኪራይ ገቢ ናቸው ፡፡ በተለይ ከጊዜ ገደብ ተቀማጭ ገንዘብና ከመንግሥት ተቀማጭ ቦንድ ያገኘው ገቢ 19.33 ሚሊዮን ብር መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ በአጠቃላይ ከልዩ ልዩ የገቢ ምንጮች ያገኘው ገቢ ከመድን ሥራ ውል ከተገኘው ትርፍ በልጦ የተገኘ መሆኑን ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ በጥቅል በሒሳብ ዓመቱ የኩባንያው ገቢና ወጪ ተሠልቶ ከታክስ በኋላ ያገኘው የትርፍ መጠን 20.05 ሚሊዮን ብር መሆኑ ታውቋል፡፡ ይህ የትርፍ መጠን ከዕቅዱም ሆነ ከቀዳሚው ዓመት ያነሰ ትርፍ ሆኗል፡፡ እንደ ኩባንያው መረጃ በሒሳብ ዓመቱ አገኛለሁ ብሎ ያቀደው 29.62 ቢሊዮን ብር በመሆኑ ከዕቅዱ 28 በመቶ የቀነሰ ስለመሆኑ በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡ የሒሳብ ዓመቱ የተጣራ ትርፍ ከቀዳሚው ዓመት የትርፍ ምጣኔ ጋር ሲነፃፀር ደግሞ የ28.21 በመቶ ቅናሽ የታየበት ሆኗ ል፡፡ ኩባንያው በቀዳሚው ዓመት አትርፎ የነበረው 27.92 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ አፈጻጸሙ ከታቀደው ጋር ሲነፃፀር የ32 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል፡፡ የውል ሥራ ውጤት መቀነስና ከዋናው መሥሪያ ቤት ሕንፃ ግዥ ጋር በተገናኘ የባንክ ወለድ ክፍያ የተመዘገበውን ትርፍ ከዕቅድ በታች እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ከዚህም ሌላ ኩባንያው ለዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ግዥ የከፈለው የባንክ ወለድ ከፍተኛ መሆን ለትርፍ መቀነስ ምክንያት እንደነበር ለመረዳት ተችሏል፡፡ ሌሎች የኩባንያውን የሥራ አፈጻጸም የተመለከተው መረጃ እንደሚያስረዳው፣ የ2012 ሒሳብ ዓመት የኩባንያው ጠቅላላ የዓረቦን ገቢ 249.4 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህም ከዕቅዱ 230.6 ሚሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር የስምንት በመ ቶ ብልጫ አለው፡፡ የቡና ኢንሹራንስ ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ዘውዱ ሚናስ ባቀረቡት ሪፖርት ላይ እንደጠቀሱት፣ ኩባንያቸው የ2012 የዓረቦን አሰባሰቡ ከዓምናው ገቢ 204.1 ሚሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር የ22 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡ በዕቅድ ዘመኑ የተከፈለ ካሳና በመጠባበቂያነት ተይዞ የሚገኝ የካሳ ክፍያ ጥያቄ መጠን 127.7 ሚሊዮን ብርና 90.9 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ በዕቅድ ከተያዘው ጋር ሲነፃፀር ደግሞ የ73 በመቶ ብልጫ እንዳለውም በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡ በዓመቱ በደረሱ ከፍተኛ የተሽከርካሪ፣ የአጓጓዥ ኃላፊነት ኢንሹራንስ አደጋዎች፣ እንዲሁም ከኮንስትራክሽን ቦንድ ዋስትና ጋር በተገናኘ ለመጠባበቂያ በተያዙ የካሳ ጥያቄዎች ምክንያት አፈጻጸሙ ከተያዘው ዕቅድ በላይ ክፍያ እንዲፈጸም ማድረጉን የቦርድ ሊቀመንበሩ አስረድተዋል፡፡ የትርፍ ምጣኔው መቀነስም በአክሲዮን ትርፍ ድርሻ ላይ ቅናሽ እንዲታይ አድርጓል፡፡ በ2012 የኩባንው አንድ አክሲዮን ያስገኘው ትርፍ 15.96 በመቶ ነው፡፡ በ2011 ግን 26.96 በመቶ ነበር፡፡ ቡና ኢንሹራንስ በ2012 ሒሳብ ዓመት ጠቅላላ የሀብት መጠኑን ወደ 630.6 ሚሊዮን ብር ማሳደጉን የጠቀሰ ሲሆን፣ በ2011 የሒሳብ ዓመት ከነበረው 420.9 ሚሊዮን ብር ሀብት ጋር ሲነፃፀር የ50 በመቶ የሀብት ዕድገት ያሳያል፡፡ በሌላ በኩል የኩባንያው ዕዳ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ 461.5 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ ዋና ዋናዎቹም በእንጥልጥል ላይ ያሉ የካሳ ጥያቄዎች፣ ለጠለፋ ዋስትና የሚከፈሉ ክፍያዎችና ጊዜያቸው ላላለቁ የዋስትና ሽፋኖች የተያዙ መጠባበቂያዎች መሆናቸውንም አቶ ዘውዱ ጠቅሰዋል፡፡ በበጀት ዓመቱ ኩባንያው የ32.6 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው ተጨማሪ አክሲዮኖች የገዛ ሲሆን፣ ኩባንያችን በዚህ በጀት ዓመት በልዩ ልዩ ተቋማት በአክሲዮን ኢንቨስትመንት ያለው የተከፈለ የአክሲዮን መዋዕለ ንዋይ 95 ሚሊዮን ብር እንደደረሰ ታውቋል፡፡ ኩባንያው ከአክሲዮን ኢንቨስትመንት በተጨማሪ አዋጭ የገቢ ማስገኛ መንገዶች ላይ አተኮሮ የሚሠራ በመሆኑ ሕግንና መመርያዎች በመከተል በባንክ የተቀመጠን ገንዘብ የተሻለ ወለድ በሚሰጡ ልዩ ልዩ ባንኮች ውስጥ አስቀምጧል፡፡ በዚህም መሠረት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ወለድ የሚታሰብበት 167 ሚሊዮን ብር ጊዜ ገደብ ተቀማጭ ገንዘብ አለው፡፡ በአጠቃላይ የኩባንያው ኢንቨስትመንቶች በበጀት ዓመቱ መጨረሻ 262 ሚሊዮን ብር ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ከኩባንያው ሪፖርት መረዳት እንደሚቻለው፣ የገበያ ድርሻ ከ18ቱ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በ13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡ ቡና ኢንሹራንስ በኢንዱስትሪው ላይ ሰባት ዓመታት ያስቆጠረ ሲሆን፣ 24 ቅርጫፎችን በመክፈት እየሠራ ይገኛል፡፡